ኢአማ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ህግ መሰረት የተመዘገቡ እና በየጊዜው ዘገባዎችን ለህዝብ የሚያቀርቡ የህትመት ፣ የበይነ-መረብ እና የስርጭት መገናኛ ብዙሃን ውስጥ በሚሰሩ አርታኢያን የተመሰረተ የሙያ ማህበር ነው፡፡ ማህበራችን ዋና አላማው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ እንዲከበር ፣ የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም የአፈፃፀም ሂደቶች እንዲሻሻሉ ውጤታማ ውትወታ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም አባላቱ እና ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን ማንኛውንም አይነት ጥቃት እንዲከላከሉ መደገፍ ፣ ጥቃቶችም ሲፈፀሙ የተጠቂዎች ድምፅ በመሆን መፍትሔ ለማስገኘት መሞገት እንዲሁም ሙያዊ ብቃት እንዲሻሻል ተግቶ መስራት ናቸው፡፡

ኢአማ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አርታኢያን በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያላቸው ወሳኝ እና የጎላ ሚና የሚገባውን እውቅና እንዲያገኝ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ለማሳካት የአባሎቹን አቅም በመገንባት ፣ በርካታ የውይይት እና የግንኙነት መድረኮችን በማዘጋጀት ፣ በአባሎቹም ሆነ በመላው የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ላይ ጥቃት እና ጫና አድራሾችን በማውገዝ እና በመሞገት እንዲሁም ለአባላት የምክር እና ድጋፍ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት እንዲከበር በትጋት ይሰራል፡፡

ኢአማ በመዝገብ ቁጥር 4527 በጥቅምት 18/2012 ዓ.ም. በኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የተመዘገበ ለትርፍ ያልተቋቋመ እና መንግስታዊ ያልሆነ የሙያ ማህበር ነው፡፡

አባልነት

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ነፃ ፣ ገለልተኛ እና የታመነ የመረጃ ፍሰት ያለው የመገናኛ ብዙሃን መፍጠር የኢትዮጵያ አርታኢያንን በአንድ መድረክ እንዲሰባሰቡ ያስቻላቸው ራዕይ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ራዕይ የወለደው ኢአማ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ላይ ወሳኙን ኃላፊነት የተሸከሙት አርታኢያን መሰባሰቢያ ጥላ በመሆኑ ከፍተኛ ኩራት ይሰማዋል፡፡

እርስዎም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ መረጃን ለህዝብ በሚያደርሱ የህትመት ፣ የበይነ-መረብ እና የስርጭት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ/የሰሩ አርታኢ ከሆኑ ፣ የዚህ ታላቅ አላማ ተጋሪ እንዲሆኑ በክብር እንጋብዝዎታለን፡፡ የኢአማ አባል መሆን ከፈለጉ ፣ እራስዎን ከዚህ በታች ከተጠቀሱት ሁለት መስፈርቶች ውስጥ ይፈልጉ፡፡

  1. መደበኛ አባል

በመደበኛ አባል መስፈርት ውስጥ የሚካተቱት አባላት ማንኛውም የአርታኢ ሙያ ደረጃ (ዋና አርታኢ ፣ አርታኢ ፣ ረዳት አርታኢ ፣ ዋና አዘጋጅ ፣ ረዳት አዘጋጅ…) ያላቸው ይሆናሉ፡፡ ተመሳሳይ የአርታኢያንን ስራ በጋዜጠኛ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ምሁራንም በመደበኛ አባልነት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፡፡

  1. የክብር አባል

ከአምስት ዓመት በላይ በአርታኢነት ያገለገሉ ፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከስራው የተለዩ የቀድሞ አርታኢያን የክብር አባል በመሆን ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ በዚህ መስፈርት ውስጥ ያሉት አባሎቻችን በማህበሩ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ላይ ድምፅ የማይሰጡ እና የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብታቸው የተገደበ ይሆናል፡፡

ማንኛውም የአባልነት ማመልከቻ ተቀባይነት የሚያገኘው በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ወቅት ሲሆን ፣ በአባልነት የሚቀላቀሉን አርታኢያን በኢአማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የአባልነት መዋጮ ይከፍላሉ፡፡

እርስዎም የኢአማ አባል መሆን ከፈለጉ ይህን ቅፅ ሞልተው እንዲያጋሩን በደስታ እንጠይቆታለን!